የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ከሚወስዱት ግማሹ ማቋረጣቸው ስጋት ፈጥሯል፡፡

በኢትዮጵያ የፀረ ኤች አይ ቪ (ኤድስ) መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር በግማሽ መቀነሱን የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ጽጌረዳ ክፍሌ (ዶክተር) የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ተጠቃሚዎችን በተመለከተ የመጣላቸው መረጃ በጣም አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ መድኃኒቱን ከሚወስዱት ውስጥ ከ50 በመቶ በታች ናቸው እየወሰዱ ያሉት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የመድኃኒት ተጠቃሚዎች ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በመፍራት ከጤና ተቋማት በመራቃቸው እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያስረዱት፡

የመረጃ ጥንቅር ችግር እንዳይሆን ለማረጋገጥም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ፣ ሁኔታው ግን አስደንጋጭ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞ እስከ አንድ ዓመት የሚሆን የፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት ክምችት እንዲኖር መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ጽጌረዳ የታካሚዎችን የጤና ተቋም ምልልስ ለመቀነስ እንደ ጤንነታቸው ሁኔታ እየታዬ ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚሆናቸውን መድኃኒት እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡ ጥንቃቄ በማድረግ መድኃኒታቸውን እየወሰዱ እንዲከታተሉም አሳስበዋል፡፡ ከኢቢኤስ አዲስ ነገር ጋር ቆይታ ያደረጉት ዳይሬክተሯ በእነዚህ ርምጃዎችና ልዩ ትኩረት በመስጠት የፀረ ኤች አይ መድኃኒት ተጠቃሚዎችን መታደግ ካልተቻለ የኤች አይ ቪ ስርጭት ከ10 ዓመታት በፊት ወደነበረበት አስጊ ሁኔታ ሊመለስ እንደሚችል ስጋት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ደግሞ የጤና ተቋማት ከኮሮና ወረርሽኝ ቀጥሎ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ የኤች አይ ቪ (ኤድስ) መከላከል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የፀረ ኤች አይ መድኃኒት እየወሰዱ የነበሩና ያቋረጡ ሰዎች ካሉ እየተለዩ በስልክ ጭምር እንዲጠሩና መድኃኒቱን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ‘‘በተለይ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የኤች አይ ቪ ምርመራ እንዲያደርጉም በትኩረት እየተሠራ ነው’’ ብለዋል ዶክተር ሊያ፡፡

ዓለማቀፍ የምርምር ውጤቶች እንደሚያመለክቱት የፀረ ኤች አይ ቪ (ኤድስ) መድኃኒት ማቋረጥ በሽታው መድኃኒቱን እንዲላመደው ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ መድኃኒቱን ወስዶ አለመፈወስን ስለሚያስከትል አደገኛ ውጤት ያስከትላል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ጤና ድርጅት በታዳጊ ሀገራት የኮሮና ወረርሽኝ ከኤች አይ ቪ፣ ወባ እና መሰል በሽታዎች ጋር በመሆን ታዳጊ ሀገራትን ክፉኛ እንዳይጎዳ ስጋቱን አስቀምጧል፡፡ በኢትዮጵያ የተስተዋለው የኤች አይ ቪ (ኤድስ) ሕሙማን መድኃኒት ማቋረጥም የዓለም ጤና ድርጅትን ስጋት ተገቢነት አመላካች ሆኗል፡፡

Share it now!