ኤችአይቪን ለመከላከል ያስችላል የተባለ መድኃኒት በአፍሪካ ሊሞከር ነው

ተመራማሪዎች የሰዎችን በኤችአይቪ መያዝን በከፍተኛ ደረጃ መከላከል ያስችላል የተባለ ግኝት ላይ መድረሳቸው ተነገረ። እንደተባለው በየሁለት ወሩ በመርፌ የሚሰጠው መድኃኒት በየቀኑ ከሚወሰዱት የጸረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች አንጻር በ89 በመቶ በሽታውን በመከላከል በኩል የበለጠ ውጤታማ መሆኑ ተነግሯል። ይህ በሙከራ ላይ ያለው በመርፌ የሚሰጠው መድኃኒት በአፍሪካ አገራት ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ሙከራ እንደሚደረግበት ተነግሯል።

በዚህም ከ3 ሺህ 200 በላይ የሚሆኑ በምሥራቅና በደቡባዊ አፍሪካ በሚገኙ አገራት ውስጥ ያሉ ለኤችአይቪ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች በመድኃኒቱ የሙከራ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "ካቦትግራቪር" በመባል ለሚታወቀው ለዚህ በመርፌ የሚሰጥ ጸረ ኤችአይቪ መድኃኒት የሚያስፈልገው የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።ይህ መድኃኒት አስካሁን በኤችአይቪ ዙሪያ ከተደረጉት የመድኃኒት ሙከራዎች ሁሉ የላቀና በበሽታው ላይ ከፍተኛ ለውጥን የሚያመጣ እንደሆነ ተነግሯል።

በመድኃኒቱ ላይ ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በሽታውን መስፋፋት ለመከላከል በየቀኑ እንክብሎችን ከመውሰድ ይልቅ አዲሱን መድኃኒት በየአራት ሳምንቱ በመወጋት በሽታውን ለመከላከል ይችላሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ኤችአይቪን ለማከም የሚውሉት ጸረ ቫይረስ መድኃኒቶች፤ በሽታውንም ለመከላከል እንደሚረዱ አመልክተዋል።ጥንቃቄ በጎደለው ወሲባዊ ግንኙነትና በደም ንክኪ በሚተላለፈው ኤችአይቪ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተያዙ ሲሆን እስካሁን ድረስም ከ32 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ተዳርገዋል።በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች ለማከምና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ጸረ ኤችአይቪ መድኃኒቶች ስላሉ በሽታው ሰበብ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ይነገራል።

Source:BBC Amharic 

Share it now!