መቅድም ኢትዮጵያ እና የጤና ሚኒስቴር የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት ዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
መቅድም ኢትዮጵያ እና የጤና ሚኒስቴር የሀገሪቱን የጤና ሥርዓት ዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
መቅድም ኢትዮጵያ ናሽናል አሶሴሽን ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተሳካ ስትራቴጂካዊ የምክክር መድረክ ማካሄዱን በደስታ ይገልጻል። በጤና ሚኒስቴር በኩል የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እና የዘርፍ ብዙ ምላሽ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ የተገኙበት ይህ መድረክ፤ መቅድም ኢትዮጵያ ወደፊት የሚያከናውናቸውን ስትራቴጂካዊ የሥራ መርሐ-ግብሮች በሀገሪቱ እየተተገበሩ ካሉ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ማሻሻያዎች ጋር ለማቀናጀትና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። በውይይቱም ማህበረሰብ-ተኮር የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው እና ሀገራዊ የጤና ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአገር በቀል ድርጅቶች ሊጫወቱ በሚገባቸው ሚናዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በምክክር መድረኩ ላይ ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ መቅድም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ግንባር ቀደምና መሪ በመሆን ላበረከተው ታሪካዊ አስተዋፅኦ እና በተለይም ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል በተደረገው ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከመነሻው ጀምሮ ለነበረው ጉልህ የመሪነት ሚና እና አሁንም እያደረገ ላለው የማይተካ አበርክቶት ምስጋና እና ዕውቅና የሰጡ ሲሆን፤ በተለይም ላለፉት 30 አመታት በላይ ያካበተውን ተግባራዊ ልምድና ሰፊ የመፈጸም አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ብሎም የኤች አይቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝባቸውን ወገኖች ቀጥተኛ የአባላት ውክልና እንዳለው ሀገር በቀል ማህበር ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማህበሩን በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በሚደደረጉ የኤች አይቪን የመከላከል እና የድጋፍ አገልግሎቶች ና በሌሎችም የጤና ዕድሎችና መድረኮች ላይ ለማሳተፍና ለመደገፍ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው አረጋግጠዋል።
መቅድም ኢትዮጵያም በበኩሉ አሁን ከሚያከናውናቸው የኤች አይቪ ተኮር አገልግሎቶች በተጨማሪም የተቀናጀ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የአገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት እና የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ሩቅና ተደራሽ ላልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ጭምር አገልግሎቱን ለማስፋፋት የጀመረውን ዝግጅት እና ስትራቴጂካዊ ሽግግር አብራርቷል።
ይህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በቀጣይ የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብ አቅምን ማሳደግ፤ በኤች አይቪ እና ሌሎች የ ማህበረሰብ-ተኮር የጤና አገልግሎቶችን ዘላቂ ማድረግ ላይ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል። መቅድም ኢትዮጵያ ናሽናል አሶሴሽን የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ላሳዩት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ፣ ጠቃሚ ምክር እና አጋርነት ያለውን ጥልቅ ምስጋና እያቀረበ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተማማኝና ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመገለጽ ይወዳል ፡፡
“ኤች አይ ቪ በደማቸዉ የሚገኝባቸዉንና በኤድስ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸዉን ወገኖች እናፍቅር! እንርዳ! እንንከባከብ”
ከመቅድም ኢትዮጵያ ናሽናል አሶሴሽን ጋር አብረው ይስሩ፤ ለተጨማሪ መረጃዎች ገጻችንን ይከታተሉ።


